በግላጭ የሚቸበቸበው ትውልድ አደንዛዥ መድኃኒት

ከሲኤምሲ ወደ አያት እየተጓዘኩ ሳለሁ ከፊት ለፊቴ ያሉ የትምህርት ቤት የደምብ ልብስ የለበሱ ሦስት ተማሪዎች ሞቅ ያለ ወሬ ይዘዋል። ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት መድኃኒታቸውን መግዛት እንዳለባቸው እያወሩ ነው::

አንዷ ተማሪ 50 ብር ከቦርሳዋ አውጥታ ፊት ለፊቷ ከሚገኘው መድኃኒት መደብር ገባች። ከገዛችው መድኃኒት ውስጥ ለሦስቱም ጓደኞቿ አንድ አንድ አነስተኛ እሽግ አከፋፈለቻቸው::

ሦስቱም ተማሪዎች በአንድነት ከእሽጉ ያወጡትን አምፒሲሊን መሰል መድኃኒት የቻሉትን ያህል ፍሬ ከማሸጊያው ላይ እየፈለቀቁ ወደአፋቸው ላኩት:: ከዚያ በኋላ ራሳቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ ተንገዳገዱና ተቀመጡ::

ሌሎች አልፎ ሂያጅ ተማሪዎች ግን እነርሱን እያዩ ይሳሳቃሉ:: መድኃኒቱን ለማወቅ ያለኝ ፍላጎት ጨመረ::

መድኃኒቱን ወደገዙበት መድኃኒት ቤት ሄጄ ሳጣራ የህመም ማስታገሻ መድኃኒት ቢሆንም የማነቃቃት ባህሪ ያለውና ሱስ የሚያስይዝ እንክብል መሆኑንና ተማሪዎች በብዛት እንደሚጠቀሙት ተረዳሁ::

ከመድኃኒት ወሳጆቹ መካከል ሐያት (ስሟ የተቀየረ) ትገኝበታለች:: አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው ዲቦራ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ናት:: ዕድሜዋ በግምት 17 ሰባት ይሆናል::

በየቀኑ አዕምሮዋ አምጪ አምጪ የሚላትን መድኃኒት ካልወሰደች ድብርትና ድካም ይጫጫ ናታል፤ አዕምሮዋ ይረበሻል::

ምክንያቱም መድሃኒቱን በተደጋጋሚ በመውሰዷ ልክ እንደ ጫት እና ሲጋራ ሱስ እንደሆነባት ትናገራለች። እሱን ካላገኘች እረፍት አይሰጣትም::

ቤተሰቦቿ ስለ ጉዳዩ ስለማያ ውቁ ሁልጊዜም ደህና እንደሆነች ያስባሉ:: እሷም ችግሯን ለመናገር አልደፈ ረችም።

ከመድኃኒቱ ጋር የተዋወቁት የዛሬ አራት ወር ገደማ እንደሆነ ትናገራለች። የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ዶናዶል የሚባል መድኃኒት እንዳለ እና እንደሚ ያነቃቃ ከሰማች በኋላ ለመሞከር ትወስናለች::

ወዲያውም መድኃኒቱን ገዝተው አምስት አምስቱን በአንድ ጊዜ ይውጡታል:: ብዙም ሳይቆዩ ሁለቱም ተዝለፍልፈው መውደቃቸውን ታስታውሳለች::

በትምህርት ቤቱ አካባቢ የነበሩ ወጣቶች በእጃቸው ላይ የነበረውን መድኃኒት ቀድሞም ስለሚ ያውቁት ደጋግፈው አንድ ጥግ ያሳርፏቸውና ምንም እንዳል ተፈጠረ «የመጀመሪያችሁ ስለሆነ ነው አይዟችሁት ለምዱታላችሁ» በሚል አበረታተዋቸው በዚህ የተጀመረው ሱስ አሁን ላይ በየቀኑ ሦስት እና አራት

የትራማዶል (ዶናዶል) እንክብሎችን እስከማስዋጥ እንዳደረሳት ትናገራለች::

በየቀኑም ከደብተር ቦርሳዋ ውስጥ በምትይ ዘው ትራማዶል የተሰኘውን መድኃኒት በትምህርት ቤት ምሳ ሰዓት ላይ ሦስት እንክብሎችን በአንዴ እንደምትውጥ ትናገራለች:: ማታም እንዲሁ ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ትደግመዋለች::

ይህ በየቀኑ የሚደረግ ልምድ ወደሱስነት እንደተቀየረ ብትረዳም ለመተው ተቸግራለች:: በየቀኑ ኪኒኑን መውሰድ ሱስ ቢሆንባትም እስከ መቼ እንደዚህ ሆና እንደምትቀጥል ግን ለእራሷም ግራ ተጋብታለች::

«አሁን አሁን ሱስ አስያዡን ከየትኛውም መድኃኒት መደብር ሸምቶ በየቀኑ የሚቅመው ተማሪ ተበራክቷል እኔ ብቻ አይደለሁም አብዛኛው ተማሪዎች ይወስዱታል» በማለት ችግሩ የእርሷ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እንደሆነ አስተውላለች::

በዚሁ መድኃኒት ባለፈው ወር ብቻ በአንድ ጊዜ አስር ተማሪዎች እራሳቸውን ስተው መውደቃቸውንም ታስታውሳለች::

መድኃኒቱ በ10 እና 15 ብር በየፋርማሲው ያለማዘዣ የሚገኝ በመሆኑ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ሳይቀሩ እየተጠቀሙት በመሆኑ አንድ መፍትሄ እንዲፈለግለት ትማፀናለች::

እኔም የሻጮቹ ያለማዘዣ እውነት መሆኑን ለማጣራት በአካባቢው ከሚገኘው አንድ የመድኃኒት መደብር አመራሁ:: ያለምንም የሐኪም ማስረጃ ይህንን ሱስ አስያዥ መድኃኒት በ15 ብር ገዝቼ ደረሰኝ ተቀበልኩ::

ከገዛሁ በኋላ ግን ፋርማሲ ባለሙያዋን እንዴት ያለ ማዘዣ ትሸጫለሽ? ብላት መልሷ አንገት ማቀርቀር ብቻ ሆነ:: ጥፋት እንደሆነ ብታውቀውም ገንዘብ ነውና በየቀኑ ለጠየቃት ሁሉ እንደምትቸበችበው ተረዳሁ:: ጉዳዩን ይዤ ወደ ተቆጣጣሪው ባለስልጣን አመራሁ::

ትራማዶል ወይም በአምራች ስሙ ዶናዶል የተባለው የመድኃኒት አይነት ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ «ሞርፊንነት» የሚቀየር መድኃኒት መሆኑን የገለጹልኝ የአዲስ አበባ_የምግብ፣ የመድኃ ኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደ ርና ቁጥ ጥር ባለስልጣን ፋርማሲስት አቶ ይመር ሁሴን ናቸው::

እንደ እርሳቸው ገለፃ መድኃኒቱ ያለ የሐኪም ማስረጃ መሸጥ የሌለበት ቢሆንም በየመ ድኃኒት መደብሩ በግላጭ እንደሚቸበቸብ ይገልጻሉ::

መድኃኒቱ ሱስ ከማስያዙ በላይ ተማሪዎቹ ላይ የጉበት እና አደገኛ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የማስከተል አቅም እንዳለው የሚናገሩት አቶ ይመር፤ መሸጥ ካለበትም በሐኪም የታዘዘለት ታካሚ ብቻ ነው::

ነገር ግን ትክክለኛ አሰራር ተከትለው የሚሸጡ መደብሮች ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ በየቦታው እየተቸበቸበ ይገኛል::

ከሚታሰበው በላይ በርካታ ተማሪዎች እየወሰዱት ያለ መድኃኒት ሆኗል:: መስሪያ ቤታቸው ጉዳዩን ተከታትሎ እርምጃ ለመውሰድ ያለው አቅም እና ክትትል ደካማ በመሆኑ በርካታ መድኃኒቶች ያለማዘዣ በመሸጥ ላይ መሆኑንም ታዝበዋል::

በመሆኑም መድኃኒት መደብሮች ያለሐኪም ማስ ረጃ የትኛውንም ዓይነት መድኃኒት እንዳይሸጡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::

የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት አስመረት ወልደብርሃን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ መድኃኒቱ «ኦፖይድ» የሚባል ሱስ አምጪ ንጥረ ነገር አለው።

መድኃኒቱ ለካንሰር ህመም፣ ለመገጣጠሚያ በሽታ፣ ከቀዶ ህክምና በኋላ እና ለሌሎችም ህመም ሲያጋጥም ስቃይን ለመቀነስ ይረዳል

በአግባቡ ለህክምና ጥቅም ሲውል በአግባቡ ይሰራል። ነገር ግን ተማሪዎች በዘፈቀደ ሲወስዱት አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት የማስከተል አቅም እንዳለው ይናገራሉ።

በመድኃኒቱ ምክንያት ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችም ልክ እንደማንኛውም የሱስ ዓይነት አስፈላጊው የሥነአዕምሮ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ከሱሱ መላቀቅ ከፈለጉም የሥነልቦና ሐኪሞች ጋር ቀርበው ተከታታይ ህክምና ማድረግ እንደሚገ ባቸው ይመክራሉ።

መድኃኒቱን በሚቋርጥበት ወቅት ምን ችግር ይደርስብኛል? ብለው ለሚሰጉም በሚሰጠው ህክምና አማካኝነት በጊዜ ሂደቶች ከሱስ ለመላቀቅ የሚያግዙ መድኃኒቶችንም ያገኛሉ።

ለአብነት ዶናዶልን ሲያቋርጡ የእንቅልፍ እጦት ካጋጠማቸው በምትኩ የእንቅልፍ መድኃኒት፤ ድብርት ካጋጠማቸው ደግሞ ዘና የሚያደርጉ ጤነኛ መንገዶችን ለአማራጭነት ከሐኪሞች ማግኘት ይችላሉ።

በመሆኑም የሱስ ተመራጭ የለውምና ተማሪዎቹ ላይ የሚታየውን ችግር ተቀራርቦ መቅረፍ እንደሚቻል ያሳስባሉ።

ጉዳዩ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ምንነት እና ስለሱስ አስያዡ መድኃኒት እና ስለተማሪዎች ግንኙነት ባለማወቃ ቸው መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም::

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም