በሃገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት መግለጫ ሰጠ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የጸጥታ አካላት፤ የሃይማኖት አባቶች፤ የሃገር ሽማግሌዎች እና ህብረተሰቡ ባከናወነው ቅንጅታዊ ስራ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመልሳለች፡፡

የነዳጅ ቦቴዎችና ሌሎች አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ የጸረ ሰላም ሃይሎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ውዥንብሮችን በማሰራጨት ህብረተሰቡ ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

ለዚህም የጸረ ሰላም ሃይሎች በሚያስተላልፉት የሁከትና ብጥብጥ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በኮማንድ ፖስቱ አሰራር መሰረት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዮ ገልጸዋል፡፡

የነዳጅ ቦቴዎችም ሆነ ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዳይስተጓገሉ ኮማንድ ፖስቱ ጥበቃ እያደረገ በመሆኑ ያለምንም ስጋትና ችግር ወደ ፈለጉበት አካባቢ መንቀሳቀስ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡

ህዝቡና ኮማንድ ፖስቱ እንዲሁም የጸጥታ አካላት በመተባበር በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና 20 ሺህ ያህል ጥይቶችንም መያዙን ተናግረዋል፡

በተለይም ከጎረቤት ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመጠንም ሆነ በአይነት እየጨመረ መምጣቱን ነው ያብራሩት፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዮ እንደገለጹት ከሆነ እነዚህ የጸረ ሰላም ሃይሎች ህገ ወጥ የጦር መሳሪዎችን ወደ ሃገሪቱ የሚያስገቡት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነትን አደጋ ላይ ለመጣል አንዲሁም በሃገሪቱ እየተከሰቱ ያሉትን አንዳንድ ግርግሮችን በጦር መሳሪያ ለመደገፍ ያለመ በመሆኑ ህብረተሰቡ አሁንም

በንቃት ሊከታተላቸው ይገባል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ ከመታወጁ በፊትም ሆነ ከታወጀ በኋላ የሻዕቢያ መንግስት የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋትን ለማድፈረስና ለማተራመስ የተለያዩ የጸረ ሰላም ሃይሎችን በማደራጀት ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ቢሞክርም በተወሰደ እርምጃ ተልዕኮው መክሸፉን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አሁንም ይህን የጥፋት ተልዕኮውን ለማሳካት ጸረ ሰላም ሃይሎችን እያደራጀ እንደሚገኝና የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ተባብሮ በንቃት ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣውን መመሪያ በመጣስ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑና ተጠርጣሪ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተለያያዘም በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል ግማሽ ያህሉ በምክር የተለቀቁ መሆናቸውንና የተቀሩት ደግሞ በጥፋታቸው ልክ ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው ተናግረዋል፡፡